Home Health / ጤና የድካም መንስኤና መፍትሄዎች

የድካም መንስኤና መፍትሄዎች

ድካም በአብዛኛው የተለመደና ከአካላዊና የአዕምሮ መድከም ጋር ተያይዞ የሚከሰት የሰውነት መስነፍና አለመበርታት ነው።

የአዕምሮና የሰውነት ድካም የተለያዩ ቢሆንም ግን አንድ ላይ ሲከሰቱ ይስተዋላል። ከኢንፌክሽን ጀምሮ እንደ ስኳር ያሉ የጤና እክሎች፣ ጭንቀት እንዲሁም በሴቶች ዘንድ ወሊድ ለድካም መንስኤ ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የሰውነት ድካም፦ የጡንቻና የሰውነት መስነፍና እንደልብ አለመታዘዝ፣ ከዚህ ቀደም ይከውኗቸው የነበሩ ቀላል ተግባራትን መከወን አለመቻል፣ ደረጃ ሲወጡ መድከምና መሰል አጋጣሚዎች የዚህ መለያ ናቸው።

የአዕምሮ መድከም፦ ትኩረት ማድረግ አለመቻል የሃሳብ መዘበራረቅ ወይም መሰረቅ እና እየሰሩ እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት።
መፍዘዝና ነገሮችን በአግባቡ አለመከወንም የዚህ ችግር ማሳያዎች ነው።

የድካም መንስኤዎች፦

የአዕምሮ ጤና ችግር፦ ከፍተኛ ጭንቀትና ውጥረት፣ የበዛ ሃዘን፣ የአመጋገብ መዛባት፣ የአልኮል እጽ ሱሰኝነት፣ በፍርሃትና ጭንቀት ከቤት አለመውጣት እና ፍቺ መፈጸም ለአዕምሮ ጤና ችግር ይዳርጋሉ።

ይህ ችግር ደግሞ ግለሰቡ በከፍተኛ ድካም እንዲጠቃ ምክንያት ይሆነዋል፤ የተጠቀሱት ችግሮች ለእንቅልፍ መዛባት ምክንያት ስለሚሆኑም ለከፍተኛ ድካም ይዳርጋሉ።

የጤና እክል፦ ከሆድና አንጀት አካባቢ ላይ የሚከሰቱ የጤና እክሎች ለዚህ ችግር ይዳርጋሉ፤ የስኳር፣ ኩላሊትና ጉበት አካባቢ በሽታዎች የዚህ ችግር መንስኤዎች ናቸው።

ከዚህ ባለፈም ከሳምባና ከልብ ጋር የተያያዙ የጤና እክሎች ለዚህ ችግር እንደሚዳርጉም ነው የሚነገረው።

ማንኛውም በሽታና ያንን በሽታ ለመከላከል በሚደረግ ህክምና መካከልም ይህ ችግር መፈጠሩ የተለመደ መሆኑንም ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።

ሌላው ግን ስር የሰደደ የጤና እክል መኖሩ፥ ድካም አሁንም አሁንም እንዲያጠቃዎት ሊያደርግ ይችላልና የህክምና ባለሙያ ማማከርዎን አይዘንጉ።

መድሃኒቶች፦ ለድብርትና ጭንቀት፣ ለአለርጂ፣ ለደም ግፊት፣ ለልብና ተያያዥ የጤና እክሎች የሚወሰዱ መድሃኒቶች እንዲሁም ከኮሊስትሮል ክምችት ጋር በተያያዘ

ለፈውስ የሚወሰዱ መድሃኒቶች ለዚህ ችግር ሊዳርጉ እንደሚችሉ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ።

የእንቅልፍ ችግር፦ በስራ አጋጣሚም ይሁን በሌላ ምክንያት የእንቅልፍ ሰዓትን ማዛባትና ማስተጓጎል ለእንቅልፍ መቆራረጥና እጦት ይዳርጋል።

የንጥረ ነገሮች እጥረት፦ በሰውነት ላይ የሚከሰት የቫይታሚን፣ ማዕድናት፣ የተበከለ ነገር መጠቀም፣ የበዛ አልኮልና አነቃቂ መጠጦችን መውሰድ ለንጥረ ነገር እጥረት ይዳርጋል።

ይህ መሆኑም ለእንቅልፍ መቆራረጥና እጦት በመዳረግ ሰውነት ላይ ድካም እንዲፈጠር ያደርጋል፤ በተለይም እነዚህ መጠጦች በመኝታ ሰዓት የሚወሰዱ ከሆነ።

ያልተስተካከለ የሰውነት ክብደት፦ ከልክ በላይ መወፈር ከፍተኛ ክብደት ከመሸከምዎ አንጻር አሁንም አሁንም ድካም እንዲሰማዎት ሊያደርግ ይችላል።

ከዚህ ባለፈም ለስኳር ህመምና ለእንቅልፍ መቆራረጥ ሊዳርግዎትም ይችላል፤ ይህ ደግሞ የሰውነትን ድካም ያባብሰዋል።

ከዚህ ባለፈም አነስተኛ የሰውነት ክብደት ያለው ሰው ጠንካራ ያልሆነ የሰውነት ጡንቻ ስለሚኖረው ለድካም ይጋለጣል።

ብዙ ወይም አነስተኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፦ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያማያደርግ ሰው ለድካም ሊጋለጥ ይችላል።

ከዚህ በተቃራኒው ግን በበዛ መልኩ ያለ ዕረፍት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግም የራሱ ችግር አለው፤ ሰውነት ከጫና ብዛት እንዲዳከም ያደርጋልና።

ይህ ደግሞ ረጅም ርቀት በሚያሽከረክሩት ላይ ይስተዋላል፤ ያለ ዕረፍት ይህን መከወን ሰውነት ከመዳከሙ የተነሳ ትኩረትን በማሳጣት ለአደጋ ሊያጋለጠው ይችላል።

ስለዚህም ያለምንም በመቀመጥ ሰውነትን ማድከም ሳይሆን በተመጠነ መልኩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ለሰውነት እረፍት እየሰጡ ስራን መከወን።

ትኩረት ማጣት፣ የጡንቻ መስነፍ፣ እጅና አይን እኩል መስራት አለመቻል፣ ራስ ምታት፣ ምናልባት መነጫነጭ፣ ነቃ አለማለት፣ ፍላጎት ማጣት፣ በቀላል ነገር መሸነፍና

መድከም፣ ማስታወስ አለመቻል፣ እንቅልፍ እንቅልፍ ማለትና በአግባቡ ማየትና ማስተዋል አለመቻል የድካም ምልክቶች ናቸው።

ችግሩን ለማስወገድ በቅድሚያ የጤናዎን ሁኔታ ማረጋገጥና ወደ መፍትሄ መምጣት ይችላሉ፤ ለዚህም በአግባቡ መተኛት መቻልና ለእንቅልፍ ሰዓትዎ አንድ አይነት ጊዜ መምረጥና መጠቀም፤ ከዚህ ባለፈም የመኝታ ቤትዎን ለመኝታ በሚመች መልኩ ማዘጋጀት።

ከመተኛትዎ ከሁለት ሰዓት ቀደም ብለው ይመገቡ።

አመጋገብ፦ በቀን በአግባቡ ሶስት ጊዜ ጤነኛ አመጋገብን መከተል፤ ከዚህ ጋር ተያይዞም አትክልትና ፍራፍሬዎችን አብዝቶ መመገብ ይመከራል።

በተጨማሪም ጤናማ ያልሆነ አመጋገብን ማስወገድና የአልኮል ፍጆታን ማስወገድም መልካም ነው።

ከአመጋገብ ጋር ተያይዞ በቂና ንጹህ ውሃ መጠጣትና ማብዛቱን ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና በአግባቡ መከወን፤ በተቻለ መጠንም ማለዳና 10 ሰዓት ከ30 እና በዚያ አካባቢ ባሉ ከመኝታ ጊዜ እስከ 3 ሰዓት በራቁ ሰዓታት ውስጥ መከወን።

እረፍት ማድረግ፦ ከማንኛውም ከባድም ይሁን ቀላል ስራ የተወሰነ እረፍት ማድረግና የተሰወነ ደቂቃ ሰውነትንና አዕምሮን ለማዝናናት መሞከርም መልካም ነው።

በዚህ መልኩ ነገሮችን ለመቆጣጠር ሞክረው ምናልባት መፍትሄ ካጡና ለውጥ ከሌለው ግን የህክምና ባለሙያ ማማከርን አይዘንጉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here