Home Health / ጤና ቦርጭን ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ለማጥፋት

ቦርጭን ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ለማጥፋት

ቦርጭ ከአመጋገብ እና በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካለማድረግ ጋር ተያይዞ ይከሰታል።

የጤና ባለሙያዎች ደግሞ የሰውነት ቅርጽና አቋምን ከማበላሸት ጀምሮ በጊዜ ሂደት ከፍ ያለ የጤና እክል እንደሚያስከትል ይናገራሉ።

የስኳር በሽታ የልብና ተያያዥ የጤና ችግሮች ቦርጭን ተከትሎ በሰውነት ውስጥ በሚከማች የስብ ክምችት ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና እክሎች ናቸው።

በአብዛኛው ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ ለቦርጭና ለሚያስከትላቸው የጤና እክሎች የመጋለጥ እድልም የሰፋ ይሆናል።

ከአመጋገብ በተጨማሪም ስኳር የበዛባቸውን መጠጦች አብዝቶ መጠጣትም ለዚህ ችግር እንደሚያጋልጥ ነው የሚነገረው።

የህክምና ባለሙያዎች ቦርጭን ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ለመቆጣጠርና ለማጥፋት የሚረዱ ምክረ ሃሳቦችንም ይሰነዝራሉ፤

አትክልትና ፍራፍሬ መመገብ፦ በውስጣቸው ለሰውነት አስፈላጊ የሆነና ለዚህ ችግር የማይዳርግ ካርቦ ሃይድሬት እንደመያዛቸው መጠን እነዚህን መመገቡ አዋጭ ነው።

ይህን ሲመገቡ ሰውነት በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን መቆጣጠርና መመጠን የሚችልበት እድልን ያገኛል።

ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች አለማብዛት፦ በአብዛኛው ለዚህ ችግር የሚዳርጉና ቅባትና ስብ የበዛባቸውን ምግቦች ከገበታ መቀነስ መልካም ነው።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፦ ይህን መከወኑ ለአጠቃላዩ ጤና ጠቃሚና አስፈላጊ ነው፤ እንደ ፑሺ አፕ እና ፑል አፕ አይነት እንቅስቃሴዎችን መከወን።

ሲት አፕ መስራት የሚመከረው በአብዛኛው ሆድ አካባቢ የተከማቸን ስብ ካሰወገዱና ከቀነሱ በኋላ ነው።

ምክንያቱም ይህ እንቅስቃሴ የሆድ አካባቢ ጡንቻን ማጠንከር እንጅ የስብ ክምችትን ለማቃጠል አይረዳምና፥ ከሲት አፕ በፊት የስብ ክምችትዎን ማቃጠል የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን በተደጋጋሚ መስራትን አይዘንጉ።

ገመድ መዝለል፣ መሮጥ፣ ውሃ ዋና እና የተመገቡትን ቅባትና የስብ ክምችት ማስወገድ የሚያስችል ከበድ ያለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መከወን ይመከራል።

ከዚህ ባለፈም ከበድ ያሉ ነገሮችን ይዞ በግማሽና ሙሉ በሙሉ ቁጭ ብድግ መስራትም መልካም ነው።

አመጋገብ፦ ከዚህ ጋር ተያይዞ ደግሞ ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች ጥሬ ስጋ ሲመገቡም ጮማ አለማብዛት እንዲሁም በዘይት የተጠበሱ የስጋ ውጤቶችን መቀነስ ይመከራል።

ቀይ ስጋ፣ የዶሮ ተዋጽኦ፣ አሳ፣ እንቁላል፣ ሳይበዛ የቅቤና አይብ ተዋጽኦዎችን እንዲሁም፥ እንደ ቆስጣ፣ ሰላጣና ጎመን የመሳሰሉ አትክልቶችን መመገብ።

በተጨማሪም ሙዝ፣ ብርቱካን፣ አፕል፣ አናናስ እና ማንጎ ጥሩ ምርጫ መሆናቸውን የህክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

በሚመገቧቸው ምግቦች ላይ የረጋ ዘይትን መጠቀም ለዚህ ጉዳት ሊዳርግ እንደሚችል ነው ባለሙያዎች የሚገልጹት።

አጃ፣ ቡኒ ሩዝ፣ ጥራጥሬዎችና ፓስታም ጥሩ የምግብ ምርጫዎች ናቸው፤ ሁሉም ግን በተመጠነ መልኩ ሊሆን ይገባል።

አልኮል አለማብዛት፦ መጠጥ ሳይበዛና በጣም በስሱ መልካም ቢሆንም ሲበዛ ግን ለጤናም ጠንቅ ይሆናል።

ምናልባት ደግሞ ስኳር የበዛባቸወን የቢራ መጠጦች የሚያዘወትሩ ከሆነ አሁንም ከቦርጭና ተያያዥ ችግሮቹ የፀዱ አይደሉም።

ድራፍትን ጨምሮ ቢራን የሚያዘወትሩ ሰዎች በአብዛኛው ቦርጫምና የሰውነት ቅርጻቸውም የተበላሸ ሲሆን ይስተዋላል፤ ይህ ደግሞ በአብዛኛው እድሜያቸው ከፍ ባሉት ላይ የበዛ ነው።

በሳምንት ከሁለት ቀን በላይ በዚህ መልኩ መጠጥ የሚያዘወትሩ ከሆነ በተቻለ መጠን ውሃ አጠገብዎ ማድረግና በሎሚ እየቀላቀሉ መጠቀም።

ከዚህ በተጨማሪም አረንጓዴ ሻይን ቢጠጡም ከዚህ ችግር ለመራቅ ይረዳወታል።

ካርቦ ሃይድሬት አለማብዛት፦ ካርቦ ሃይድሬት አስፈላጊ ቢሆንም በተቻለ መጠን መጠኑን ዝቅ ማድረግ ይገባል።

ምናልባት ቀጭን ነኝ ብለው ይህን ለመቀየር እየሞከሩ ከሆነ፥ ድንች፣ ፓስታ፣ ነጭ ሩዝ እና ዳቦን አለማብዛት ይሻላል።

እነዚህን መመገብ ካለብዎት ከበድ ያለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከከወኑ በኋላ ቢሆን ይመረጣል፤ በአንጻሩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በመመገብ ክብደትዎን ማስተካከል ይችላሉ።

ፕሮቲን፦ ፕሮቲን የበዛባቸውን ምግቦች ጥቂት በዛ ማድረጉ ሰውነት የስብ ክምችቱን እንዲቀንስ ይረዳዋልና ይጠቀሙበት።

ምናልባት ቦርጫምና የስብ ክምችት ያስቸገረዎት ከሆኑም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እያደረጉ ጥቂትና ቀላል ምግቦችን መመገብ።

ይህን ሲያደርጉ ሰውነት ያወጣውን ሃይል ለመተካት የስብ ክምችቱን ያቃጥላል በዚያውም ጥንካሬን ይሰጥዎታል፤ ግን በጣም እስከሚራቡ ድረስ ነገሮችን ማድረግ አይመከርም።

ምን ጊዜም ቢሆን ሰውነት የስብ ክምችት አያስፈልገውም አይባልም፥ ዋናው ነገር ቅባቱና የስብ ክምችቱ በዝቶ አደጋ ላይ እንዳይጥልዎት መጠንቀቁ ላይ ነውና ሰውነትን በደረቅ ምግቦች ብቻ መጉዳትም አይገባዎትም።

ሁሉንም በተመጠነ መልኩ ማድረግና ጤናማ አመጋገብን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማጀብን አይርሱ።

ቁርስ መመገብ በተቻለ መጠን በየሶስት ሰዓቱ ቀላል ፍራፍሬ ቢመገቡ ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ በኋላ ደግሞ ካርቦ ሃይድሬት የበዛባቸውን ምግቦች ማዘውተር።

ከምግብ በኋላ ሁለት ብርጭቆ ውሃ መጠጣት ባለሙያዎች አስፈላጊ ብለው ያሰፈሯቸው ናቸው።

ጤናማ አመጋገብን ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጋር አዋህደው ክብደትዎን መቆጣጠርና መከታተልንም አይዘንጉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here