Home News / ዜና 12ኛው የኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ተከበረ።

12ኛው የኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ተከበረ።

12ኛው የኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ተከበረ።

በዓሉ “በህገ መንግስታችን የደመቀ ህብረ ብሄራዊነታችን ለህዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል በሰመራ ስታዲየም በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል።

በበዓሉ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የፌዴራል እና የክልል የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

እንዲሁም የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር፣ የጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌህ እና የሶማሊያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር መሃዲ መሃመድ ቡሌን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።

የአፋር ክልል ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርእሰ መስተዳደር ሀጂ ስዩም አወል የመክፈቻ ንግግር በማድረግ በዓሉን ያስጀመሩ ሲሆን፥ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

12ኛው የኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በተሳካ መልኩ እንዲከበር ለተባበሩ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ያለው አባተም፥ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ለበዓሉ ታዳሚዎች አቅርበዋል።

አቶ ያለው በንግግራቸው፥ የዘንድሮው ኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የሰው ዘር መገኛ በሆነችው የሉሲ መንደር በአፋር ክልል መከበሩ ለበዓሉ ልዩ ድምቀት መስጠቱን አንስተዋል።

አቶ ያለው፥ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ብዝሃነትን ተቀብሎ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የመገንባትን ግብ በማድረግ፥ ለሁለንተናዊ ለውጥ መሰረት ጥሏል ብለዋል።

በዚህ ሳይወሰን ፈጣን ልማት እንዲመዘብ በማድረግ የመጣውን ለውጥ ህዝቡ ተጠቀሚ እንዲሆን ያስቻለ መሆኑንም ተናግረዋል።

“የፌደራል ስርዓታች ራስን በራስ እና ሀገርን በጋራ ማስተዳደር ያስቻለ ነው” ያሉት አቶ ያለው፥ “ዜጎች የጋራ ጉዳያቸውን በሚመለከት በፌዴራል ስርዓት የሚተዳደሩበት እና በየአካባቢያቸው ደግሞ ራሳቸውን የሚያስተዳደሩበትን ነፃነት ያቀዳጃቸ ነው” ብለዋል።

“ህገ መንግስቱ ይህንን ሁኔታ በመፍጠሩ ትግላችን ድህነት እና ኋላ ቀርነት ላይ በማተኮር ባለፉት ዓመታት ባለብዙ መገለጫ ድሎች ተመዝግበዋል” ሲሉም ተናግረዋል።

ይህ እንዳለ ሆኖ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ህግ መንግስታዊ ስርዓቱን በሀይል ለመናድ የሚደረጉ መፍጨርጨሮች እየተከሰቱ መሆኑንም አቶ ያለው ገልፀዋል።

በጥልቅ ተሃድሶው ከህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ አለመፈታታቸው እንዳለ ሆኖ፥ ከኪራይ ሰብሳቢነት የሚነሱ ድክመቶችን መነሻ በማድረግ በህዝቦች መካከል ግጭቶችን ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ያለ የሌለ ሀይላቸውን በመጠቀም በፌደራል ስርዓቱ ላይ ዘምተዋል ብለዋል።

ከሚያቀራርቡን እና ከሚያግባቡን ጉዳዮች ይልቅ ልዩነቶቻችን ላይ ብቻ እንድናተኩር እና እርስ በእርሳችን በጥርጣሬ እንድንተያይ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም ያሉት አቶ ያለው፥ በግለሰቦች መካከል የሚነሱ ግጭቶችን ሳይቀር የብሄር መልክ በማላበስ የግጭቶች ምንጭ የፌደራል ስርዓቱ አስመስሎ በማቅረብ ሊለያዩን ይሞክራሉ ሲሉ ገልፀዋል።

“በአፈፃም የሚያጋጥሙ እንከኖችን እየቀረፍን የምንከተለው ስርዓት ይበለጥ እንዲጎለበት በማድረግ የሁላችንም ሃላፊነት ነው” በማለት አሳስበዋል።

“የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህንን የጥፋት ሀይሎች ሴራ ተገንዝበው ሊያወግዟቸው እና ሊታገሏቸው ይገባል” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሎች መካከል የተጀመሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች ተጠናክረው እና ጎልተው እንዲካሄዱ በማስቻል ዴሞክራሲያዊ አንድነት ይበልጥ እየጎለበተ እና የህዝቦች ቅርርብ እየደረጀ እንዲሄድ ማድረግ እንደሚገባም ገልፀዋል።

“አሁን ባለንበት የትግል ምእራፍ ውስጥ ሆነን እስካሁን ያስመዘገብናቸውን ድሎች በመጠበቅ እና አንድ የኢኮኖሚ ፖለቲካ ማህበረሰብ እና ጠንካራ የፌደራል ስርዓት ለመገንባት ከመቼውም ጊዜ በላይ ርብርብ ማድረግ ይኖርብናል” ብለዋል።

በፌደራል ስርላቱ ላይ የተደቀኑትን የስራ አጥነት ችግር፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራረን እንዲሁም ህዝባዊ አንድነትን የሚንዱ የተዛቡ አስተሳሰቦችና ተግባራትን በማስተካከል ሀገራዊ ራእያችንን ለማሳካት መረባረብ አለብን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በዓሉ በተሳካ መልኩ እንዲከበር ላደረጉ ለአፋር ክልል ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፣ የአፋር ክልል ህዝቦች፣ የክልል መንግስታት፣ ምሁራን እና ባለሀብቶችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አዲስ በተነገባው የሰመራ ስታዲየም በመከበር ላይ በሚገኘው በዓል ላይም የኢትዮጵያ የብሔሮች ብሔረሰቦች የባህል አምባሳደሮች ባህልን የሚያንፀባርቁ ዜማዎችን በማሰማትና ባህላዊ ውዝዋዜዎችን በማሳየት ለበዓሉ ድምቀት ሰጥተዋል።

እንዲሁም የጁቡቲ የባህል ልኡካን 12ኛው የኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ላይ በመገኘት የተለያዩ ትርኢቶችን አቅርበዋል።

በዓሉ እንዲሳካ ላደረጉ አካላት እንዲሁም በበዓሉ ላይ በክብር እግድነት ለተገኙ አካላት የምስጋና እና የእውቅና ሽልማት ተበርክቷል።

በተያያዘ ለአንድ ዓመት በደቡብ ክልል የቆየው የኢትዮጵያ ህዳሴ ዋንጫም ለቀጣይ ተረኛ ክልል ተላልፎ ተሰጥቷል።

የደቡብ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፥ የህዳሴ ዋንጫ በክልሉ በነበረው ቆይታ በህብረሰተዙ ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳት መፍጠሩን ተናግረዋል።

የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በክልሉ በ1 ዓመት ቆይታው 500 ሚሊየን ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ በህብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ ከ1 ቢሊየን 768 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ገልፀዋል።

ዋንጫው ወደ ክልሉ ከመምጣቱ በፊት በክልሉ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ 733 ሚሊየን ብር ተሰብስቦ እንደነበር የገለጹት አቶ ደሴ፥ በአጠቃላይ በክልሉ እስካሁን ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ከክልሉ ህዝብ መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

አቶ ደሴ በመጨረሻም ዋንጫውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ያስረከቡ ሲሆን፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ዋንጫውን ለኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሃመድ ኡመር አስረክበዋል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሃመድ ኡመርም፥ ዋንጫው በክልሉ በሚኖረው ቆይታ ከክልሉ ህዝብ ጋር በመሆን ለህዳሴው ግድብ ገቢ የማሰባሰብ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በመጨረሻም የቀጣይ የኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አዘጋጅ በምረጥ የበዓሉ አከባበር ተጠናቋል።

የ13ኛው የኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አዘጋጅም አዲስ አበባ ከተማ ሆና ተመርጣለች።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here