Home News / ዜና ያልታመመ ልጇን ታሟል እያለች ወደ 323 ሆስፒታሎች ያስመረመችው እናት አነጋጋሪ ሆናለች

ያልታመመ ልጇን ታሟል እያለች ወደ 323 ሆስፒታሎች ያስመረመችው እናት አነጋጋሪ ሆናለች

ያልታመመ ልጇን ታሟል እያለች በ323 ሆስፒታሎች ምርመራ እንዲያደርግ እና 13 ቀዶህክምና ያሰራችለት እናት አነጋጋሪ ሆናለች።

ነገር ጠምዛዥ የሚል መለያ የተሰጠላት ይህች እናት ያለምንም ምክንያት ልጇን ታሟል እያለች ለህክምና 323 ሆስፒታሎችን ማዳረሷ ብዙዎችን እያስገረመ ነው።

በርካታ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያደርጉትን ማንኛውንም ነገር በልጆች ፍላጎት ላይ ተመስርተው ነው የሚፈፅሙት።

በአሜሪካ የቴክሳስ ነዋሪዋ ካይሌኔ ቦውን ራይት ግን ሃኪሞችን ልጇ በማይድን በሽታ መታመሙን ለማሳመን እየሞከረች ጤናማ ልጇን በ323 ሆስፒታሎች እንዲንከራተት አድርጋዋለች።

በዚህም መሰረት እናተየዋን ያመኑ ሃኪሞች ለታዳጊው 13 ጊዜ ቀዶ ህክምና ያደረጉለት ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት ለህይወቱ ስጋት በሚፈጥሩ ህመሞች ተጠቅቷል።

የስምንት ዓመቱ ታዳጊ ክርስቶፈር በህይወቱ ያለፉትን ዓመታት ያሳለፈው በሆስፒታሎች ነው።

ክርስቶፈር የሆስፒታሎችን መርገጥ የጀመረው ገና እንደተወለደ ሲሆን፥ ይህም ጉዞ በአውሮፓውያኑ እስከ 2015 ድረስ ቀጥሏል።

የቴክሳስ የህፃናት ሆስፒታል የእናቱ የመዝገብ ቁጥር እና የተገኘው የምርመራ ውጤት የልጁን ጤናማነት የሚያሳይ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ የክርስቶፈር መንከራተት አብቅቷል።

በዚህም የሆስፒታሉ ሰራተኞች ለህፃናት የጥበቃ አገልግሎት በመደወል እናት ቦውን ህፃኑን እንዲጎዳ አድርጋለች በሚል እንድትታሰር አድርገዋል።

የ34 ዓመቷ እናት ልጇ ለከፍተኛና ለማይድን ህመም ተዳርጓል በሚል ቀዶ ህክምና እንዲደረግለት ለማሳመን ሃኪሞችን መዋሸቷን አምናለች።

በምርምራ ሂደት በተገኘ መረጃ መሰረት ይህ ወላጅ እናት ማጭበርበር ወንጀል የጀመረው ከመደበኛው ጊዜ ቀድሞ የተወለደው ክሪስቶፈር የ11 ወር ህፃን በነበረበት በ2009 ነው።

እናቱ ቦውን ልጇ የወተት አለርጂ አጋጥሞታል በሚል ግምት ለስምንት ዓመታት ያህል በተለያዩ ሆስፒታሎች ለህክምና እንዲሄድ አድርጋለች።

በዚህም ሃኪሞችን በመዋሸት የጨረራ፣ የቀዶ ህክምና እና ሌሎችንም የህክምና ሂደቶችን እንዲያልፍ አድርጋለች።

በክስ ሂደትም አባቱ ሪያን ክራውፎርድ እና እናት ቦውን ተከራክረዋል።

በዚህም እናት ሃኪሞች ልጇ መንቀሳቀስ እንደማይችል እንደነገሯት፣ ልጇ የመመገቢያ ቱቦ ሊገጠምለት እንደሚገባ መወሰናቸውን ነግረውኛል የሚል ሀሳብ ለዳኞች አቅርባለች።

ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም ቦውን ልጇ ለማይድን የካንሰር ህመም መዳረጉን በመግለፅ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ ጀመረች።

ሆኖም በፈረንጆቹ 2015 የህፃናት ጥበቃ አገልግሎት ልዩ መርማሪዎች ህፃኑ ወደሚገኝበት ቤት ያመራሉ።

በዚህም ህፃኑ የኦክሲጅን ማስክ ተገጥሞለት ያገኙታል።

ሆኖም ህፃኑ ክሪስቶፈር ለልዩ መርማሪዎች ባለፈው ዓመት ከወንድሙ ጋር ሲጫወት እንደነበር፥ ትምህርት ቤት ሲሄድም የቅርጫት ኳስ ጨዋታ ያደርግ እንደነበር እና ጤነኛ መሆኑን ነገራቸው።

በዚህም መሰረት መርማሪዎች ህፃኑን ወደ ሆስፒታል ይወስዱታል፤ ምርመራ ሲደረግለትም ሙሉ ጤነኛ ሆኖ ያገኙታል።

በምርመራ ውጤቱም ያለምንም የመመገቢያ ቱቦ እንደማንኛውም ሰው መመገብ እንደሚችል፣ ኦክስጅን እንደማያስፈልገው ይረጋገጣል።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮም በህፃኑ ላይ ምንም ዓይነት የጤና እክል አላገጠመውም፥ እናቱ በዚህ ህመም ታሟል እያለች ያሟረተችበት ሁሉ ህመም ሳይከሰት ይቀራል።

በእርግጥ ክርስቶፈር በምርመራ ሙሉ ጤናማ ሆኖ ቢገኝም እናቱ የፈጠረችው ምናባዊ ህይወት አእምሯዊ ጫና እንደፈጠረበት ተነግሯል።

የክርስቶፈር አባት በፃፈው ማስታወሻ ልጁ ጤናማ ሆኖ ታሟል በሚል የስቃይ ዓመታትን ማሳለፉ እንዳሳዘነው ገልጿል።

ታዳጊው ያልምንም ማስረጃ ሃኪሞች መታመሙን ለማረጋገጥ በሰሩለት 13 ቀዶ ህክምና ምክንያት ሶስት ጊዜ ህይወቱን የማጣት ስጋት ተጋርጦበት እንደነበር ነው አባቱ የተናገረው ።

ክሪስቶፈር አሁን በህፃናት የመንከባከቢያ ማዕከል ድጋፍ እየተደረገለት ነው።

እናቱ ቦውን ያንን ድርጊት በልጇ ላይ የፈፀመችው ሙንቻውሰን( Munchausen Syndrome by Proxy) ለሚባል እና በአሳዳጊ ምክንያት በሚፈጠር ህመም ወይም ጉዳት ለአዕምሮ ህመም መዳረግን ለሚያመለክተው አዕምራዊ ችግር ሰለባ በመሆኗ ነው ተብሏል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here