Home News / ዜና አሜሪካ የፀጥታው ምክር ቤት በኢየሩሳሌም ላይ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ አደረገች

አሜሪካ የፀጥታው ምክር ቤት በኢየሩሳሌም ላይ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ አደረገች

አሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢየሩሳሌም ላይ ያሳለፉትን ውሳኔ ለመቃወም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ አደረገች።

በምክር ቤቱ የአሜሪካ ቋሚ ተወካይ ኒኪ ሃሌ ሀገራቸው ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ናት በሚል የሰጠችውን እውቅና ለመቃወም በግብፅ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውድቅ ማድረጓን ተናግረዋል።

የውሳኔ ሀሳቡ አሜሪካን በስም ባይጠቅስም የኢየሩሳሌምን ጉዳይ በተመለከተ የተሰጠው ውሳኔ ህጋዊ መሰረት የሌለው እና ውድቅ መደረግ ያለበት ነው ይላል።

ከአሜሪካ ውጭ ሌሎች 14 የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት የውሳኔ ሀሳቡን ደግፈው ድምፅ ሰጥተዋል።

በምክር ቤቱ የአሜሪካ ቋሚ ተወካይ ኒኪ ሃሌ የውሳኔ ሀሳቡን “ዘለፋ ነው” በሚል የገለፁት ሲሆን፥ መቼም ቢሆን የማንረሳው ብለውታል።

“የአሁኑ የውሳኔ ሀሳብ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእስራኤልና የፍልስጤን ግጭት ለመፍታት ከመልካም ነገር ይልቅ ጎጂ ድርጊቶችን እየፈፀመ መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ ምሳሌ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።

“ዛሬ ኤምባሲያችንን የት ማድረግ እንዳለብን ያሳየንበት እና አሜሪካ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር የተገደደችበትን ውሳኔ ነው ያደረገችው፤ ይህን ስናደርግም በኩራት ነው” ብለዋል።

ትራምፕ በኢየሩሳሌም ላይ ያሳለፉት ወሳኔ ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያንን ወደ ግጭት ከቷቸዋል።

ፍልስጤማውያኑ ምስራቅ ኢየሩሳሌምን የወደፊቷ ሀገራችን ዋና ከተማ ናት ብለው ያስባሉ።

ሆኖም የኢየሩሳሌም ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔም በሁለቱ ወገኖች መካከል በሚደረግ የሰላም ድርድር ላይ ስምምነት ላይ ሊፈታ እንደሚችል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያምናል።

የውሳኔ ሀሳቡ የበለጠ ድጋፍ ለማግኘት በሚመስል ሁኔታ የኢየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማነት ለመቃወም በያዘው ጭብጥ ላይ አሜሪካ ወይም ትራምፕ የሚል ንጥል ቃላትን አልተጠቀመም።

ከዚህ ይልቅ ሁሉም ሀገራት በቅድስቷ ከተማ በኢየሩሳሌም የዲፕሎማሲ ተልዕኮ መስሪያ ቤቶችን እና ኤምባሲዎችን እንዳይከፍቱ ጥሪ አቅርቧል።

የፍልስጤም አስተዳደር ቃል አቀባይ የአሜሪካ ውሳኔ ተቀባይነት የሌለው እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዳይረጋጋ የሚያደርግ በሚል ገልፀውታል።

የፍልልስጤሙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪያድ አል ማሊኪ በበኩላቸው፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉበኤ እንዲያደርግ ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል።

የአሜሪካ ቋሚ ተወካይ በፀጥታው ምክር ቤት ላደረጉት ውሳኔ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔትያንያሁ ምስጋናቸውን ገልፀውላቸዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here